Saturday, March 28, 2015

የሶሻል ሚዲያ በገጠር ለሚኖሩ ያለው ፋይዳ - Social Media in Rural Ethiopia (Yem Special Wereda)

የሶሻል ሚዲያ በገጠር ለሚኖሩ ያለው ፋይዳ! በመጀመሪያ የሶሻል ሚዲያ (Social Media) ምንድን ነው? የሶሻል ሚዲያ ማለት አንድ ህብረተሰብ ባልተደራጀ መልኩ ዜናን የሚቀያየርበት የመረጃ መቀያየሪያ መድረክ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል:: ሶሻል ሚዲያ የኢንተርኔት ወይም የመረጃ መረብ ሚዲያ አይነት ሲሆን ከባህላዊና የተለመደው ሚዲያ በተሻለ የተቀላጠፈ መልኩ ግንኙነትን መፍጠር የሚያስችል፣እንዲሁም አሳታፊም የሆነ መደረክ ነው:: የሶሻል ሚዲያ ምሳሌች- ፌስቡክ፣ትዊተር፣ኢንስታግራም፣ዩትዩብ ዋነኞቹ ናቸው። ይህ ሚዲያ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍሎች ለሚኖሩ ምን አይነት አስተዋፅዖ ሊኖረው ይችላል?
የብሮድባንድ ያለመስፋፋት የሶሻል ሚዲያን ሊገድበው ይችላልን? የሶሻል ሚዲያን ለመጠቀም የተለየ ትምህርት መማር ያስፈልጋልን? የሶሻል ሚዲያ ከባህላዊው የማስ ሚዲያ በምን ይለያል? ገበሬው በዚህ ወቅት የሶሻል ሚዲያ ለመጠቀም ዝግጁ ነውን? የሶሻል ሚዲያ ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ አለውን? የሶሻል ሚዲያ ዲሞክራሲን የማለምለምና አንባገነንነትን የማዳከም ባህሪ አለውን? የሶሻል ሚዲያን የማስፋፋት የማን ሃላፊነት ነው? የሶሻል ሚዲያን የኛ ሰው እንዴት በሚገባ መጠቀም ይችላል?

Technological Advancement - What can we contribute? ቴክኖሎጂና የኛ አስተዋጽኦ

ቴክኖሎጂና የአንድ ሃገር እድገት ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው:: ቴክኖሎጂ የሚገዛ ብቻ ሳይሆን ትኩረት ከተሰጠው አገር ውስጥ ሊተከል፣ሊበቅልና ሊያድግ የሚችል ነገር ነው:: ዛሬ ዓለማችን የደረሰችበት ማንኛውም ዓይነት እድገት ምንጩ ቴክኖሎጂያዊ መነሻ አለው:: ቴክኖሎጂ  የሚለው ቃል ከግሪክ ቃል "ቴክኒ" የተገኘ ሲሆን በግሪክ "ጥበብ፣ችሎታ ወይም የእጅ ስራ" ማለት ነው:: ቴክኖሎጂ የቴክኒኮች ጥርቅም፣ምርትንና አገልግሎትን የምናመርትበት ወይም ደግሞ ሌሎች ግቦችን በቀላሉ የምንመታበት ዘዴ ወይም ሂደት ነው:: ቴክኖሎጂ የቴክኒክ ወይም የሂደት እውቀት ሊሆን ይችላል:: በሌላ መልኩ ደግሞ ማሽን፣ኮምፒውተር፣ፋብሪካ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች  ውስጥ ተደብቆ የሚገኝ ነገር ሊሆን ይችላል::

የሰው ልጅ ቴክኖሎጂን መጠቀም የጀመረው ገና ጥንት የተፈጥሮ ሃብትን ወደ ቀላል መሳሪያዎች መቀየር ሲጀምር ነው:: በጥነተ ታሪክ የሰው ልጅ እሳትን ያገኘበት ሁኔታ ለምሳሌ የሚጠቀስ ነው:: በቅርቡ ከምናውቃቸው ቴክኖሎጂያዊ እድገቶች፡የማተሚያ መሳሪያ፣ስልክ፣ኢንተርኔት፣ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው::
ሁሉም ማህበረሰብ ወይም ግለሰብ ለሰው ልጆች ሊያበረክተው የሚችላቸው ቴክኖሎጂዎች ይኖራሉ:: በኢትዮጲያ ታሪክ ለምሳሌ የህንፃ ግንባታ ቴክኖሎጂዎችና ውጤታቸው በአክሱም፣ላሊበላ፣ሃረር፣ እና ጎንደር በስፋት ታይቷል:: የእርከን ቴክኖሎጂ በኮንሶ ታይቷል:: የሙዚቃ ስርአቶች በያሬድ ተዘርግተዋል:: ዛሬ ታዲያ የምንጠይቀው ጥያቄ እኛ ለሰዉ ልጆች ወይም ለኢትዮጲያ ህዝቦች ብሎም ለራሳችን የሚጠቅም ምን ዓይነት ቴክኖሎጂን አበረከትን የሚል ነው:: ይህ ጥያቄ ግለሰብንም ማህበረሰብንም የሚመለከት ስለሆነ ልናስብበት የሚገባ አይመስላችሁም?

ወደ መሬት ስናወርደው፣ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ህይወት አብዮታዊ በሆነ መልኩ ሊቀይር የሚችል መሆኑ ታውቆ፣በመጀመሪያ ስነልቦናዊ ብሎም ምሁራዊና ቴክኒካዊ ዝግጅትን በግለሰቦችና ባጠቃላይ ማህበረሰብ ወስጥ መፍጠር ያስፈልጋል:: የአንድ ማህበረሰብ ዕድገት ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ማህበረሰቡ ለቴክኖሎጂ ያለው ግንዛቤ ብሎም የራሱን ችግር በራሱ ልጆች በተፈጠሩ አዳዲስ ነገሮች መፍታት ሲችል ወይም የመፍታት አቅምን ሲያዳብር ነው:: እኛ ራሳችንን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመቀበልም ሆነ የፈጠራ አስተዋጽኦ ለማድረግ ምን ያህል በግለሰብምና በማህበረሰብ ደረጃ አዘጋጅተናል?

ቴክኖሎጂን ቀላል፣መካከለኛና ከባድ ብለን በመክፈል ማየት እንችላለን:: ትላልቅ ቴክኖሎጂውች በጣም ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ብሎም ብዙ ጥልቅ ምርምርን የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ:: ለምሳሌ የሮኬት፣የሳተላይት፣የአውሮፕላን ቴክኖሎጂዎችን ትልቅ ወይም ከባድ ቴክኖሎጂ ሊባሉ ይችላሉ። በአንጻሩ ደግሞ መካከለኛ የምንላቸው ቴክኖሎጂዎች እንደኛ ባሉ አዳጊ ሃገራት በግለሰብ ደረጃም ባይሆን በመንግስት ሊተገበሩ የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ የመኪና፣ባቡር፣የህክምና ቴክኖሎጂዎችን በዚህ ክፍል ልንመድባቸው እንችላለን። በዋናነት ግን ለኛ በአብዛኛው በዚህ ጊዜና ሁኔታ የሚጠቅመንና ልናተኩርበት የሚገባው ቀላል ወይም አነስተኛ ተብለው የሚታወቁትና መሰረታዊ የሆኑት ቴክኖሎጂዎች ላይ ነው። አብዛኛው የኛ ማህበረሰብ በእርሻ ስራ ላይ የተሰማራ በመሆኑ ምግብን በብዛትና በጥራት ለማምረት የሚያስችል ማንኛውም ቴክኖሎጂ ሊተኮርበት የሚገባ ነው::

ቴክኒካዊ ብቃትን በማህበረሰባችን ውስጥ ለማስረጽ፣ ህጻናትን ከታች ጀምሮ መቅረጽን ይጠይቃል። በተለይ በሂሳብና በተፈጥሮ ሳይንስ ጥናት ትኩረት ሰጥተን ልናስታጥቃቸው ይገባል። በተለይ የኛን ችግሮችን መቅረፍ የሚችሉ አድርገን ልናዘጋጃቸው ያስፈልጋል።